Insight Detail Banner

The Game plan

The Power of the Chief Emotional Officer (CEO) | በቤተሰብ ቢዝነሶች ውስጥ “የዋናው የስሜት መኮንን” ወሳኝ ቦታ

By Originally authored by Ivan Lansberg and Translated by Zekrie Negatu, December 2025

Authors

Author

Originally authored by Ivan Lansberg and Translated by Zekrie Negatu

Ivan Lansberg is a Founding Partner at Lansberg Gersick Advisors and Zekrie Negatu is a Managing Director at HST

የቤተሰብ ንግዱ መስራች አባወራ ሥልጣን እየቀነሰ ሲሄድ የህይወት አጋሩ የሆነችው የእናት ድምፅ በተተኪነት ዕቅድ ውስጥ ያላት ሚና ወሳኝ እየሆነ ይሄዳል።

 

በቅርቡ አንድ ትልቅ የሶስተኛ ትውልድ የአውሮፓ ኩባንያ ዓመታዊ ባለአክሲዮኖች ስብሰባ ላይ እንድሳተፍ ተጋብዤ ነበር። የዚህ ስብሰባ ዋነኛ የትኩረት ነጥብ የነበረው የኩባንያው መስራች ባለቤት የሆኑት አዛውንት ሴት ከታደሙት ባለአክሲዮኖች መካከል መገኘት ነበር። እኚህ የ95 ዓመት ባለ ግርማ ሞገስ እመቤት በሚያስደንቅ ሁኔታ የጠራ አስተሳሰብ ያላቸውና ማራኪ ተናገሪ ነበሩ። ከተሽከርካሪ ወንበራቸው ላይ ሆነው ለ36ቱ የቤተሰብ ወራሾች እና የትዳር ጓደኞቻቸው ያደረጉት ንግግር እኔ በህይወቴ ከሰማኋቸው በጣም ልብ ከሚነኩ ንግግሮች ውስጥ አንዱ ነበር።

 

እኚህ እድሜ ጠገብ እማወራ (matriarch) ስለ ቤተሰብ አስፈላጊነት እና በቀደሙት ትውልዶች ስለተደረጉት ስፍር ቁጥር የሌላቸው መስዋዕትነቶች በሚያምር አነጋገር ተናገሩ። ባለቤታቸው ከአቅራቢዎቻቸው እና ከደንበኞቻቸው ጋር በፍትሃዊነትና በአክብሮት ለመስራት ያደረጉትን ጥረት አስታወሱ። እንዲሁም ሁለቱን አስከፊ የዓለም ጦርነቶች ጨምሮ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን ሁሉንም ዕዳቸውን ለመክፈል የነበራቸውን የማያወላውል አቋም እና ትጋት ገለጹ። ቀጥለውም የኩባንያው መስራች ከመሞታቸው በፊት ለልጆቻቸው የተናገሩትን፡ “ብዙ ገንዘብ አልተውላችሁም፣ ነገር ግን መልካም ስም ትቼላችኋለሁ — በጥበብ ተጠቀሙበት” ያሉትን የመጨረሻ መልዕክት በማስታወስ ተረካቢው ትውልድ የቤተሰቡን መልካም ስም እንዲጠብቅ አሳሰቡ፡፡ በተጨማሪም፣ የቤተሰብ አባላት ንግዱን እንደ ንግድ አድርገው እንዲመለከቱት፣ ነገር ግን ደግሞ “ዋና ንብረቶቻቸው በየምሽቱ ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚሄዱት [የኩባንያው ሠራተኞች] መሆናቸውን እንዳይዘነጉ” አጥብቀው መከሩ። በመጨረሻም፣ “ቅናት እና ምቀኝነትን” ከመቀስቀስ ውጭ ፋይዳ ሰለሌለው፣ ሐብታቸውን ለሌሎች ለማሳየት እንዳይጥሩ ለሚወዷቸው ሰዎች አስጠነቀቁ።

 

ንግግራቸውን ሲጨርሱ፣ መላው ቤተሰብ በጦፈ እና በማያቋርጥ ጭብጨባ ከወንበሩ ተነስቶ አክብሮቱን ገለጸላቸው።

 

ከአዛውንቷ እመቤት ንግግር በኋላ እኒህ ሴት ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ይህ ኃይለኛ እና ነባር የንግድ ቤተሰብ እንዴት ይቀጥል ይሆን? እያልኩ ማሰላሰል ጀመርኩ። እርሳቸው በሌሉበት የቤተሰብነት መንፈሱን ማን ሊያስቀጥለው ይችላል? እርሳቸው ሲጫወቱት የነበረውን የአማካይነት ቦታ እና ሚና እርሳቸው በማይኖሩበት ጊዜ በእጅጉ በተስፋፋው የቤተሰብ ቅርንጫፎች መካከል ያለውን ስውር ፉክክር ቤተሰቡ እንዴት ሊወጣው ይሆን? እያልኩ ለራሴ ጥያቄዎችን ደረደርኩ፡፡ በአጭሩ፣ እኔና ባልደረቦቼ “የቤተሰብ ዋና የስሜት መኮንን (CEO—“Chief Emotional Officer”) ብለን የምንጠራውን ሚና ሌላ ሰው ተክቶ ሊይዝ ይችል ይሆን? እያልኩ በሐሳብ ነጎድኩ፡፡ 

 

በትውልድ መተካካት እቅድ ውስጥ የእናቶች ሚና

የቤተሰብ ኩባንያዎች ቀጣይነት አጀንዳ ሲነሳ ብዙውን ጊዜ ትኩረቱ በንግዱ ውስጥ ባለው የአመራር ተተኪነት ላይ ይሆናል። ነገር ግን፣ የሎዮላ ቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባዬ የሆነው ጆን ዋርድ እንደሚለው፣ የአንዳንድ የቤተሰብ ቢዝነስ ሥርወ-መንግሥታት (family business dynasty) መውደቅ ብዙውን ጊዜ የሚመጣው በእናትየው ሞት እንጂ በአባትየው ሞት አይደለም።

ለዚህ በርካታ ምክንያቶች አሉ።


በአብዛኞቹ ባህላዊ ቤተሰቦች ውስጥ ለቤተሰብ ግንኙነቶች ቃና የምትሰጠው እናት ነች። ምርጥ እና መንፈሰ ጠንካራ ሴቶች በሚቀጥለው ትውልድ አባላት መካከል የእኩልነት፣ የትብብርና የመተሳሰብ ስሜት አንዲሰፍን ከጀርባ ሆነው የሚያበረታቱ ናቸው። ወንድም እና እህቶች አብረው የሚሠሩበትን መሠረት ይጥላሉ። ልጆች አድገው በንግዱ ውስጥ ቢሠሩም እንኳ ተጽዕኖአቸው ጠንካራ ሆኖ ይቀጥላል። ይህ ተጽዕኖ ሲጠፋ ንግዱን ሊያበላሹ የሚችሉ አጥፊ ፉክክሮች ሊቀሰቀሱ ይችላሉ።


ምንም እንኳን በአሁኑ ዘመን ሴቶች ሰፋ ያለ የሕይወት ምርጫ አና የራሳቸው የሥራ መስክ ሊኖራቸው ቢችልም፣ በአብዛኞቹ ቤተሰቦች ውስጥ የባህላዊው የሥራ ክፍፍል ፈጽሞ አልጠፋም። በእነዚህ ቤተሰቦች ውስጥ እናቶች ከአባቶች ይልቅ በልጆቻቸው ላይ የበለጠ መሠረታዊ ተጽዕኖ አላቸው። እንደ ዋና ተንከባካቢነታቸው ብዙውን ጊዜ የቤተሰቡ ቢዝነስ ሥርወ-መንግሥት ህልሞች ዋና አርክቴክቶች ናቸው። ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ልጆቻቸውን በሕይወት ምርጫቸው፣ የሚመሩበትን መሠረታዊ እሴቶችንና የሥራ ምኞቶችን ይቀርጹላቸዋል። የልጆችን የኑሮ ዘይቤ፣ ተስፋዎች እና ለሥራ እና ለሐብት ያላቸውን መሠረታዊ አመለካከቶች ይቀርጻሉ።


የአሉታዊ ተጽዕኖ ዕድሎች

እርግጥ ነው፣ የእናት ሚና አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ፈርጅ ሊኖረው ይችላል። ለምሳሌ እናት በቤተሰብ ንግድ ውስጥ መሥራት በጥረት እና በብቃት የሚገኘ መብት ሳይሆን በመወለድ የሚገኝ መብት እንደሆነ ለልጆቿ የምታስተላልፍ ከሆነ የወደፊት እድገታቸውን ሊያግድና ንግዱን ሊጎዳ የሚችል የይገባኛል ስሜትን (sense of entitlement) ሊያዳብር ይችላል።


በቅርቡ የምትወደው ልጇ ከኮሌጅ እንደተመረቀ ወዲያውኑ ወደ ቤተሰብ ንግድ እንዲገባ አጥብቃ በመጠየቅ የሚፈለገውን ስሜታዊ ብስለት እንዳያገኝ የከለከለች እናት አጋጥማኝ ነበር። ሴትየዋ በዕድሜ የገፋው ባለቤቷ ንግዱን የቤተሰብ አባል ላልሆነ ሥራ አስፈጻሚ አሳልፎ ለመስጠት እያሰበ እንደሆነ ፈርታ/ጠርጥራ ነበር። ልጁ እንደተመረቀ ወደ ንግዱ ካልገባ እንደ ተተኪ ያለውን ከመወለድ የሚመነጭ መብት ሊያጣ ይችላል ብላ ሰግታ ነበር። ሰለዚህ እናትየዋ አዲስ የኮሌጅ ተመራቂ የሆነውን ልጇን የስራ ልምዱን ሊያበለጽጉና በረጅም ጊዜ ውስጥ ለአመራር በተሻለ ሊያዘጋጁት የሚችሉ ሌሎች ቦታዎች የመሥራት እድሎችን እንዲተው አሳመነችው።


የእናትነት ሚና በሽግግር ወቅት

ወንዶች የንግድ ባለቤቶች በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ በባለቤቶቻቸው ላይ የበለጠ ጥገኛ ይሆናሉ። የባል ሥልጣን ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሲሄድ የእናትየዋ ድምፅ ይበልጥ አስፈላጊ ይሆናል፣ ክብደቱም ይጨምራል።በመሆኑም የትውልድ ሽግግር ጊዜው ሲቃረብ እናቶች በሚቀጥለው ትውልድ የንግዱ አሠራርና መዋቅር ላይ ወሳኝ ሚና መጫወት ይጀምራሉ። የባላቸውን የጡረታ ዕቅዶች በማበረታታት ወይም ባለማበረታታት የአመራር በትረ ስልጣናቸውን የሚያስረክቡበትን ፍጥነት ሊያፋጥኑ ወይም ሊያዘገዩ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ በተግባር የሚታየው ሁኔታ ደግሞ ቀድሞ የታሰበበት የተተኪነት ዕቅድ ተግባራዊ አንዳይደረግ ተፈጥሯዊ ዳተኝነት ከሚያሳዩት ባሎቻቸው ጋር በመተባበር ሽግገርን መቃዎም ወይም ማዘግየት ነው።


ምንም እንኳን እናቶች መደበኛ የኩባንያ ሚና ባይኖራቸውም የተለያዩ ልጆቻቸው ያላቸውን አንጻራዊ ብቃት እና ሐላፊነት የመውሰድ ዝግጁነት ለመወሰን በሚደረገው ግምገማ ላይ ጉልህ በሆነ መንገድ ተጽዕኖ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይህ ተጽዕኖ የዕጩ ተተኪዎችን ደረጃ እስከማስለወጥ ድረስ ሊሄድ ይችላል።


እንደ ምሳሌ በአንድ የምህንድስና ድርጅት ውስጥ በጣም ብቃት ያላት ሴት ልጅ አባቷን ለመተካት ተሰልፋ ነበር። ነገር ግን በሴቶች ሚና ላይ ባህላዊ አመለካከት የነበራት እናቷ ልጇ “በወንዶች ዓለም ውስጥ ስኬታማ ለመሆን” የምታደርገውን ጥረት መደገፍ አልቻለችም። እናትየዋ በሥራዋ ምክንያት ልጇ ባሏንና ልጆቿን ችላ እያለች እንደሆነ በተደጋጋሚ ታማርራለች። በመጨረሻም፣ ልጂቷ በአንድ ጊዜ ጥሩ ወላጅ አና ውጤታማ የንግድ መሪ መሆን እንደምትችል ወላጆቿን — በተለይም እናቷን — በፍፁም ማሳመን እንደማትችል ተሰምቷት ኩባንያውን ለቅቃ ወጣች።


ወሳኝ የትብብር ፍላጎት

በቤተሰብ ንግዶች ጉዳይ ላይ የተለያዩ የአስተሳሰብ ጎራዎች ቢኖሩም ለጤናማ የቤተሰብ አሠራር ምን የስፈልጋል በሚለው ጥያቄ ላይ ግን ብዙ ስምምነት አለ፡፡ ይሄውም ባልና ሚስት ቤተሰቡን በጋራ፣ እንደ አንድ ቡድን መምራት አለባቸው የሚለው ሐሳብ ነው። የቤተሰባቸውን ኩባንያ ልጆቻቸው እንዲረከቡ ለሚፈልጉ ወላጆች ደግሞ ይህ በተለይ እውነት ነው። የሚፈለገውን ቁርጠኝነት ለማዳበር ወላጆች ስለ ንግዱ ያላቸውን ራዕይ በግልጽ እርስ በእርሳቸው እንዲሁም ልጆቻቸው ነፍስ ማወቅ ሲጀምሩ ከእነሱ ጋር መወያየት አለባቸው። ወደፊት ሊነሱ የሚችሉ ግጭቶችን ለመቀነስ የወላጆች ህልሞች ግልጽ እና የተጣጣሙ መሆን አለባቸው።


ለቤተሰብ ንግድ ባለቤቶች የትምህርት መርሃ ግብሮችን ስነድፍ እና በኩባንያው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሌላቸውን እናቶች እንዲሳተፉ ስመክር አሁንም ተቃውሞ ይገጥመኛል። “እርሷ በንግዱ ውስጥ በፍጹም ምንም ሚና የላትም” እባላለሁ። “ለምን እርሷን በማይመለከታት በንግድ ጉዳዮች በሚያጠነጥን ፕሮግራም ላይ እንድትሳተፍ ያለአግባብ ገንዘብ እናባክናለን?” የሚል ጥያቄ ይቀርበልኛል፡፡


ሌላው ቢቀር ይህ አይነቱ አስተያየት “በአብዛኛው ሚስቶች ከባሎቻቸው ይበልጥ በህይዎት የመቆየት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው የሚለውን እስታቲስቲካዊ እውነታ” የሚዘነጋ ነው። ብዙውን ጊዜ ሴቶች ከባሎቻቸው ህልፈት በኋላ በንግዱ ውስጥ ተቆጣጣሪ ድምጽ ያላቸው ባለድርሻ ይሆናሉ እናም ድንገተኛ ሁኔታ ሲፈጠር ስለወደፊቱ ጊዜ ወሳኝ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ይጠየቃሉ።


እነዚህን በቤተሰቡ ንግድ ውስጥ ወደፊት ወሳኝ ሚና ሊኖራቸው የሚችሉ ሴቶችን ለጊዜው በቢዝነሱ ውስጥ ተሳትፎ የላቸውም በማለት ስለ ንግዱ ፍላጎቶች በደንብ መማር አያስፈልጋቸውም ብሎ መደምደም ከባድ ስህተት ነው። የቤተሰብ ንግድን ቀጣይነትን የማቀድ ጉዳይ ሲነሳ የባለቤቶች እና የእናቶች ተሳትፎ ተፈላጊ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ነው። ልክ ታሪካቸው በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ ላይ እንደተጠቀሰው ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጠው እንዳየናቸው አዛውንት ሴት እነርሱ የቤተሰብ ኩባንያው ልብ እና ዋና የስሜት መኮንኖች - አንዳንድ ጊዜም የቤተሰቡ የስሜት ሰርኪዩት ብሬከር - ናቸው።

……………..

ኢቫን ላንስበርግ፣ በኒው ሄቨን ሲቲ የሚገኝ ድርጅታዊ የሥነ ልቦና ባለሙያ ሲሆን፣ በአሜሪካና በውጪ ካሉ ብዙ የቤተሰብ ንግዶች ጋር ይሠራል።

Source: Family Business Magazine, Spring 1995. Printed with permission from the author, Ivan Lansberg.

How can we help?

Get in touch with us
Hst logo

HST works with clients to solve business growth, operational, people, financial, tax, governance, risk, learning and compliance challenges with locally relevant solutions.

Join Our Newsletter

Follow us on

Contact

Addis Ababa: Ethio-China Friendship Ave,
Mina Building 4th and 5th Floor

Addis Ababa Tel: +251 115 52 76 66/67

Adama: Gurmu Woreda around Mebrat Hayle,
Oromia Bank building 2nd Floor

Adama Tel: +251915156522/+251911866404

info@hst-et.com

P.O. Box 25701


@2025 HST. All Right Reserved